ከንቱነት
ሰባኪው እንዲህ ይላል “ሁሉ ከንቱ የከንቱ ከንቱ ነው።” እንዲህ ብሎ የተናገረው ጠቢቡ ሰለሞን ፤ እንደርሱ ያለ ጠቢብ ከእርሱ በፊትም ሆነ ከእርሱ በኋላ አይነሳም የተባለለት ነው። ከእርሱ በኋላ የመጣን ፍጥረታት ደግሞ በጥያቄዎች ተሞልተን ለጥቂቱ መልስ አግኝተን ለጥቂቱ ደግሞ እናገኛለን በሚል ተስፋ ተሞልተን መልስን እየሻን ወደ ጉድጓዶቻችን እንሄዳለን ፤ ወደ ጎሬአችን እንወርዳለን። የእኔ አመለካከት “ሁሉ” በሚለዉ ቃል ውስጥ የሰው ልጆችን ያጠቃልላል የሚል እሳቤ የለኝም ምክንያቱም “ሰውን በመልካችን ፤በአምሳላችን እንፍጠር “ ሲባል በፈጣሪው አምሳል ውስጥ ከንቱነት አይገኝም።ከፈጣሪው ማንነት ጋር ስለማይሄድ ከንቱ የሆነበት ጊዜ ከሌለ ደግሞ ከንቱ (ቢሆን እንኳ) የሚሆንበት ጊዜ ተጀምሯል ልንል ነው፤ ይህ ደግሞ አንድን ባህርዩ ካለመሆን ወደ መሆን ሊመጣ ማለት ነው። ይህን ሀሳብ በሁለት ምክንያቶች እንጥለዋለን ማለት ነው፤ ከጊዜ እና ከባህርይ አንፃር ።ስለዚህ የወረስነው መልክ ከንቱ አይደለም፤ሰውም ከንቱ አይሆንም ነገርግን ለከንቱነት ተላልፎ ተሰጥቷል ፤ውድቀት ሲጀምር ከንቱነት ተጀመረ። ከንቱነት የጀመርነው እኛው ፍጥረቶቹ ነን። የሰው ልጅ ይሁን ሳጥናኤል እና ግብረአበሮቹ በውድቀት ከንቱነትን “ሀ” ብለው ጀመሩ። ሌላኛው ሀሳብ እዚህ ላይ የምናነሳው ከንቱነት ከውድቀታችን ጋር የተሰጠን በልባችን እንዲኖር ነው ወይስ ወደ ከንቱዋ አለም ተጥለን ከንቱነትን ተምረን ነው? መለማመድ አዕምሮአችን ውስጥ ተቀረፀ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተላለፈ ፤ ተያይዞ የመጣው ትውልድ የከንቱነትን ጥልቀት በደምብ ወደውስጥ ገብቶ ጠፍቷል ፤ ለዚህም ነፃ የሚወጣበት መሰላል ያስፈልገዋል።
ከንቱነት በደረጃ የተከፋፈለ ይመስለኛል እንደ አጠቃላይ በአንፃራዊነት ከሌላ ባህል ወይም ከሌላ ቦታ አንፃር ስመለከተው ሲያንስ እና ሲበዛ አስተዋልኩ ነገርግን መለኪያዬ ከሰውነት ውጪ ሊሆን አይገባም ምክንያቱም ባህል፣ሀሳብ ወይንም አመለካከቶች ፣ ህግጋት እና ወግ የሚባሉት ነገሮች የሰው ልጆች ለከንቱነት ተላልፈው ከተሰጡበት የመነጨ ስለሆነ እነዚህ ነገሮች መለኪያ ሊሆኑ አይችሉም ይሁኑ እንኳን ብን፤ ከእኔ አንፃር ይህ ነው መለኪያው እያለ ሁሉም የራሱን ከሌላው አንፃር ሲታይ የተዛባ ነገርን ይፈጥራል። ስለዚህ ከንቱነት በሞላት በዚህ ዓለም የመጣን እኛ ከዚህ ከንቱነት ከፍ ብሎ ያለውን በመመልከት የተፈጠርንበትን አላማ እንመልከት።

